የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ በአንድ አገር ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት ውስጥ ጠቃሚ ሚና የሚጫወት መሆኑ እሙን ነው፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የቴሌኮም ዘርፍ የሚሰጠውን ዘርፈብዙ ጠቀሜታ በመገንዘብ በሀገሪቱ ውስጥ የኢንፎርሜሽንና ኮመኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንዲል በማድረግ በዓለም አቀፈ ደረጃ ተወዳዳሪና በክፍለ አህጉሩም ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዲኖረው ለማስቻል እንዲሁም  ዓለም አቅፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት ለሁሉም በያለበት በመስጠት በመረጃ የበለፀገ ሕብረተሰብ እንዲገነባ በማድረግ ይህ የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ የሚጫወተውን ቁልፍ ሚና የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል::
 በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ በአንድ በኩል በየጊዜው እያደገና እየተለዋወጠ ከሚሄደው ከወቅቱ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ እድገት ጋር አብሮ ለመጓዝና በሀገሪቱ የቴሌኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለውጥ ለማምጣት በሌላ በኩል ደግሞ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሕብረተሰቡን የዘመናዊ ቴሌኮም ፍላጎት ለማርካት ግዙፍ የካፒታል በጀት በመመደብ ነባሩን የቴሌኮም አገልግሎት ከማጠናከር በተጨማሪ የተለያዩ እና ዘመናዊ የሆኑ የሚቀጥለው ትውልድ ኔትዎርክ የቴሌኮም ኘሮጀክቶችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
 
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነባ ካለው መጠነሰፊ የቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ጋር የተጣጣመ የዓለም አቀፍ መገናኛ መኖር አስፈላጊ  እና ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ተልዕኮውን ለማሳካት ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛ ለሆነው ለኢንተርኔት፣ ለድምጽና ለዳታ አገልግሎት ዓለም አቀፍ መገናኛ ሥራ ላይ የሚውል እጅግ ከፍተኛ፣ ፈጣንና አስተማማኝ የኔትወርክ አቅም ያለው ዓለም አቀፍ የባህር ጠለቅ የፋይበር ኬብል Submarine Cable መገናኛ መስመር በ47 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 634.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ለመዘርጋት የሚያስችል የስምምነት ውል በኮርፖሬሽኑ እና ሲኮም SEACOM በተባለ የቴሌኮም ኩባንያ መካከል ተፈርሟል፡፡
ይህ የስምምነት ውል የተፈረመበት ዓለም አቀፍ የባህር ጠለቅ የፋይበር ኬብል Submarine Cable መገናኛ መስመር 20 STM-1 3,100 ሜጋ ባይት በሰከንድ ጠቅላላ የኔትወርክ አቅም ያለው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 16 STM-1 2,480 ሜጋ ባይት በሰከንድ የሚሆነው የኔትወርክ አቅም ለኮርፖሬሽኑ የንግድ ተግባራት የሚውል ሲሆን ቀሪው 4 STM-1 620 ሜጋ ባይት በሰከንድ የኔትወርክ አቅም ደግሞ ለE-Government አገልግሎት የሚውል ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ይህንን የመገናኛ ማስፋፊያ ውል ከሲኮም ጋር የተዋዋለበት ምክንያት ኩባንያው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገሮችን  በህንድና በአውሮፖ በኩል ከቀሪው ዓለም ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ከፍተኛና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የባንድዊድዝ አቅም ያለው በመሆኑና ለኘሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የተጠየቀው ወጪም ከሌሎች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ወጪዎች ጋር ሲነጻጸር  ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
ይህ አዲስ የስምምነት ውል የተገባበት የዓለም አቀፍ መስመር ማስፋፊያ ውል ኮርፖሬሽኑ በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚሠጣቸውን አገልግሎት የበለጠ ለማሣደግና ለደንበኞቹ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ነው፡፡
በዚህም መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡትን የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና እና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የበለጠ ለማጠናከርና ለደንበኞቹም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ይሆናል፡፡
የሲኮም ኩባንያ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራትን ከሌላው ዓለም ጋር በተመጣጣኝ ዋጋ ለማገናኘት የሚያስችል 1.28 ቴራ ባይት በሰከንድ /17,ዐዐዐ ኪ.ሜ/ ባህር ጠለቅ ዓለም አቀፍ የግንኙነት መስመር አቅም ያለው ኩባንያ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሲኮም ዓለም አቀፍ የግንኙነት መስመር ጋር ከተገናኙ የአፍሪካ አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ይገኙበታል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ለዓለም አቀፍ ግንኙነቱ በኦኘቲካል ፋይበር 537 ሜጋ ባይት በሰከንድ፣ በሳተላይት 342.4 ሜጋ ባይት በሰከንድ እና በማይክሮዌቭ 18 ሜጋ ባይት በሰከንድ በድምሩ 897.4 ሜጋ ባይት በሰከንድ አቅም እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ይህ ከሲኮም ጋር ስምምነት የተደረሰበት ዓለም አቀፍ የባህር ውስጥ የፋይበር ማስፋፊያ ውል ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት አሁን አገሪቱ የምትጠቀምበት 537 ሜጋ ባይት በሰከንድ የኦኘቲካል ፋይበር የኔትወርክ መገናኛ አቅም ወደ 3,637 ሜጋ ባይት በሰከንድ በማሳደግ በ677.3 በመቶ እንዲጨምር እንዲሁም በማይክሮዌቭ፣ በሳተላይትና በፋይበር አማካኝነት ለዓለም አቀፍ መገናኛ የሚያገለግለው ጠቅላላ 897.4 ሜጋ ባይት በሰከንድ የብሮድባንድ ኔትወርክ ጌትዌይ አቅም ደግሞ በ445.44 በመቶ ከፍ እንዲል በማድረግ በዘርፉ ታላቅ ጠቀሜታ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ የፋይበር ግንኙነት በሀገሪቱ ውስጥ ፈጣንና አስተማማኝ የሆነ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መስመር ኔትወርክ እንዲስፋፋ፣ ጠንካራ ዓለም አቀፍ የግንኙነት መረብ እንዲፈጠር፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ፕሮግራም እንዲጎለብት በተለይም ደግሞ ኮርፖሬሽኑ በቬንደር ፋይናንሲንግ አማካኝነት የሚያካሒዳቸው የሚቀጥለው ትዉልድ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ የቴሌኮም ኘሮጀክቶች በአጠቃላይ የኦኘቲካል ፋይበር ኘሮጀክት ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ለህበረተሰቡ ለመስጠት የታቀደው እቅድ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲሳካ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡
 
በውጤቱም ሀገሪቱ የዘመናዊ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ገቢ እንዲጨምር፣ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኝ ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የስኩልኔት፣ የወረዳኔት፣ የአግሪኔት፣ የርቀት ትምህርት፣ የጤና አገልግሎቶች የበለጠ እንዲስፋፉ፣ አስተማማኝ የቴሌቪዥን ስርጭት እንዲኖር ወዘተ እና ከሁሉም በላይ መንግስት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን የቀየሰው የልማት ግብ እንዲሳካ በማድረግ በቀጣይ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ በቁርጠኝነት የሚደረገው ጥረት በአስተማማኝ ሁኔታ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በማድረጉ ረገድ የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡
 
ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽ ኮርፖሬሽን
መጋቢት 9 ቀን 2002 ዓ.ም