የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የሰሜን አዲስ አበባ ዞን ጽ/ቤት በዞኑ ስር ከሚገኙ ደንበኞች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ ጥር 2ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በግዮን ሆቴል አካሔደ፡፡
በዕለቱ የተካሔደውን የምክክር መድረክ ዓላማ አስመልክተው በኮርፖሬሽኑ የመንግስትና ደንበኞች ግንኙነት ም/ዋና ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ውብሸት ተክሌ እንደገለፁት፣ በምክክር መድረኩ ደንበኞች አጋጠሙን የሚሉዋቸውን ቅሬታዎች እና አስተያየቶች በግብዓት መልክ በመውሰድ የኮርፖሬሽኑን ቀጣይ እርምጃ ለማሳካት እና ከደንበኞች ጋር መልካም የስራ ግንኙነት ለመፍጠር በማሰብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ የዞኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ /ሎካል ስዊቺንግ/ አቶ ተካበ ኪዳኔ ዞኑ የሚሸፍናቸውን አጎራባች ክልሎች ለታዳሚዎች የገለፁ ሲሆን፣ በስሩም በርካታ የመደበኛ ስልክ፣ የሞባይል፣ የኢንተርኔት እና ሌሎች ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ደንበኞች እንዳሉት አመልክተዋል፡፡ ምክትል ስራ አስኪያጁ በገለፃቸው ወቅት እንዳሉት፣ ዞኑ በተለያዩ ጊዜያቶች ባጋጠሙት የኬብል ስርቆቶች፣ በተለያዩ የኮንስትራክሽን ስራዎች በሚከሰቱ የኬብል መቆረጥ አደጋዎች እና በቅርቡ በአራዳ ቴሌ ከፍተኛ አካባቢ ጽ/ቤት ላይ ባጋጠሙ የእሳት ቃጠሎ ችግሮች የተነሳ ለመስጠት ያቀዳቸውን አገልግሎቶች በተሟላ መልኩ ለማሳካት አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ አቶ ተካበ በመጨረሻም መድረኩ በዋነኛነት በዞኑ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን በቀጣይ ዘላቂነት ባለው መልኩ በመፍታት የተሻለ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ማቅረብ እንዲቻል መስመር ለማስያዝ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች የቀረቡ የተለያዩ ገለፃዎችን ካዳመጡ በኋላ ተሳታፊዎች ከሰነዘሩዋቸው አስተያየቶች እና ጥያቄዎች መካከል፣ ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ የጀመረው የዘመናዊነት ጉዞ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልፀው፣ ያም ቢሆን የተወሰኑ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡ ለአብነት ያህልም አይ.ኤስ.ዲ.ኤን /ISDN/ አገልግሎቶችን ለማግኘት ክፍያ ቢፈጽሙም አገልግሎቱን አለማግኘታቸውን ገንዘባቸውም ተመላሽ አለመደረጉን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የጥገና እና ሌሎች አገልግሎቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለመጠየቅ ወደ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ቢደውሉም ስልክ እንደማይነሳ፣ የአገልግሎት ሒሳብ ክፍያን በተመለከተ "ከተጠቀምነው አገልግሎት በላይ ክፍያ ተጠይቀን ክፍያውን ከፈፀምን በኋላ የአሰራሩን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ ምርመራ እንዲደረግልን ስንጠይቅ ለመመርመሪያ ተጨማሪ ክፍያ እየተጠየቅን ስለሆነ ያለአግባብ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረግን ነው" ሲሉ አንዳንድ ተሳታፊዎች ቅሬታቸውን የገለፁ ሲሆን በተጨማሪም፣ የጥገና አገልግሎት በጠየቁት የጊዜ ፍጥነት እና የሥራ ጥራት መሠረት ማግኘት አለመቻላቸውን፣ የብልሽት አገልግሎት ለማስመዝገብ ብሎም መረጃ ለማግኘት ወደ ኮርፖሬሽኑ የ997 የጥሪ ማዕከል ቢደውሉም ምላሽ ለማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያ በሽያጭ እና የተለያዩ የስራ አካባቢዎች የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የኮርፖሬሽኑን አገልግሎቶች እንዲገነዘቡ እና ለደንበኞች አስፈላጊውን መረጃ መስጠት የሚችሉበትን መንገድ ኮርፖሬሽኑ ቢያመቻች ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም አልፎ አልፎ ምክንያቱ በውል በማይታወቅ ሁኔታ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚቋረጥ በዚህም የተነሳ አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን እና ኮርፖሬሽኑ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ቢያበጅ አሊያም ምክንያቶችን በፍጥነት ቢያሳውቀን የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄና አስተያየቶች በተሳታፊዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተካሒዷል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ቴዎድሮስ አጥላው የኤን.ጂ.ኤን ኘሮጀክት አስተባባሪ የኮርፖሬሽኑን የኤን.ጂ.ኤን. ኘሮጀክት አጀማመር እና ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ የተመለከተ ገለፃ ለታዳሚዎች ያቀረቡ ሲሆን፣ በገለፃቸውም ወቅት ኮርፖሬሽኑ በዚህ ኘሮጀክት አማካኝነት የጂ.ፒ.አር.ኤስ /GPRS/ ኢ.ዲ.ጂ.ኢ. /EDGE/፣ ደብሊው.ሲ.ዲ.ኤም.ኤ /WCDMA/ እና ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶችን ለማሳካት በከፍተኛ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም ፊክስድ ላይን ኤን.ጂ.ኤን /FIXED - LINE NGN/ የተባለውን አገልግሎት እውን ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎች ተከናውነው በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች አገልግሎቱ የተጀመረ መሆኑን እና በሰሜን አዲስ አበባ ዞን ክልል ውስጥ የመረጃ ዝውውር /Data Migration/ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡ የሲ.ዲ.ኤም.ኤ /CDMA_WLL/ እና ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶች ዝርጋታ ስራም ቀደም ሲል በመጠናቀቁ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አቶ ቴዎድሮስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ወደ 1ዐ,ዐዐዐ ኪ.ሜትር አካባቢ የሚያካልል የፋይበር ኬብል ዝርጋታ ስራ መጠናቀቁን በዚህም የኮርፖሬሽኑን የቴሌኮም አገልግሎት መረጃ የመሸከም አቅም ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር መቻሉን፣ በቅርቡ በርካታ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል የቢሊንግ ሲስተም መጠናቀቁን፣ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ሲሰራበት የነበረውን የጥሪ ማዕከል ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ የሚቀጥለው ትውልድ የጥሪ ማዕከል /Next Generation Call Center/ የተሰኘ ዘመናዊ የጥሪ ማዕከል አስገንብቶ ማጠናቀቁን አቶ ቴዎድሮስ ለታዳሚዎች አብራርተዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑን የብሮድባንድ አገልግሎት አሰጣጥ የተመለከተ ገለፃ ለታዳሚዎች ያቀረቡት አቶ አማረ አሰፋ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል የነበረው የብሮድባንድ አገልግሎት ከነበረበት የአቅም ውስንነት የተነሳ በተወሰኑ የሀገሪቱ ከተሞች እና ክልሎች ብቻ ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ችግሩን ይቀርፋል ተብሎ በሚገመተው የአይ.ፒ ኤን.ጂ.ኤን /IP-NGN/ አገልግሎት መጀመር የተሻለ አገልግሎት ይቀርባል የሚል እምነት በኮርፖሬሽኑ በኩል እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም በአንዳንድ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ላይ ከደንበኞች አያያዝ ጋር በተያያዘ የስነ ምግባር ችግር ሊስተዋል እንደሚችል የገለፁት አቶ አማረ፣ ሠራተኞች በደንበኞች አያያዝ በኩል ሊያዳብሩ በሚገባቸው የስራ ባህሪ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስያዝ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በመጨረሻም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የአገልግሎት መቋረጥ ችግሮች ከፋይበር ኬብል መቆረጥ ጋር የተያያዙ ስለሚሆኑ ኮርፖሬሽኑ ብቻውን ችግሮቹን ሊቆጣጠር እንደማይችል ነገር ግን ከህብረተሰቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት ዘላቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ኮርፖሬሽኑ ጥረት ያደርጋል ሲሉ አቶ አማረ አብራርተዋል፡፡
የዞኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተካበ ኪዳኔ በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ላይ ከተሳታፊዎች አጽንኦት ተሰጥቶባቸው በተደጋጋሚ የተነሱ የኬብል ዝርጋታ፣ የመስመር ጥገና አገልግሎት አሰጣጥ እና ሌሎች በምክክር መድረኩ የተነሱ በርካታ ጥያቄዎችን በመውሰድ አፋጣኝ መፍትሔ እና ምላሽ ለመስጠት ኮርፖሬሽኑ እና ዞኑ በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀው መድረኩ ተጠናቋል፡፡