የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም ቫት ተመዝጋቢ እና የ2ዐዐ1 ዓ.ም. ግብር የከፈሉ የድህረ ክፍያ ወይም ባለመስመር ሞባይል አገልግሎት ፈላጊዎች ያለምንም ዋስትና ወይም የገንዘብ መያዣ አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
 
      በዚሁ በኮርፖሬሽኑ ውሳኔ መሠረት ያለ ቫውቸር ካርድ የሚሠራ የድህረ ክፍያ ሞባይል አገልግሎት ፈላጊ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም ቫት ተመዝጋቢ ወይም ከፋይ ስለመሆናቸው የማረጋገጫ ሰነድ በማቅረብ ብቻ ሌላ ተጨማሪ መስፈርት ሳይጠየቁ ከማንኛውም የኮርፖሬሽኑ የሽያጭ ማዕከላት በድርጅታቸው ስም ወይም የድርጅቱ ባለቤት ሆነው በስማቸው ከፈለጉም በስማቸው አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡ በዚህም ውሣኔ መሠረት የንግድ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ኤምባሲዎች የዚሁ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
 
      ቀደም ሲል ባለው በኮርፖሬሽኑ አሠራር መሠረት የድህረ ክፍያ ወይም የባለመስመር ሞባይል ስልክ አገልግሎት የሚያገኙት የትላልቅ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወይም ታዋቂ ግለሰቦች ወይም VIP የሆኑ ብቻ ከድርጅታቸው የድጋፍ ደብዳቤ እና ዋስትና ሲያቀርቡ ሲሆን፤ በግለሰብ ደረጃ አገልግሎቱ አይሰጥም ነበር፡፡
 
ቀደም ሲል በነበረው አሠራር የድህረ ክፍያ ሞባይል ስልክ አገልግሎት ለመ/ቤት ወይም ለድርጅት ሲጠየቅ፡-
·     የድርጅቱ የንግድ ሥራ ፈቃድ ወይም የኢንቨስትመንት ሰርተፍኬት ሲቀርብና ከብር 15,000 ያላነሰ ካፒታል ያለው ወይም  ብር 15,000 በጥሬው ተቀማጭ ማድረግ ወይም፣ ብር 15,000 ዋስትና ከኢንሽራንስ ድርጅት ማቅረብ ይኖርበት ነበር፡፡ በአሁኑ በኮርፖሬሽኑ ውሳኔ መሠረት ግን እነዚህ የተጠቀሱት የዋስትና መስፈርቶች እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡  
 
 
   የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን
    ጥር 13 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.