ETC News    
   
     WHO IS WHO
     CHECK MAIL
     VACANCY
     YELLOW PAGES
     FEEDBACK
     FAQs
 
Dialing Codes
   
Interurban Dialing Code
  Essential Numbers
  International Dialing Codes
 
Websites at Ethiopage
   
 
 
 
  ጋዜጣዊ መግለጫ


ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የቅድመ ክፍያ ሲምካርዶች እና የቅድመ ክፍያ ማስደወያ ካርዶችን በተለያዩ የንግድ ተቋማትና ማህበራት አማካይነት ለደንበኞች በውክልና የማከፋፈል/የሽያጭ አገልግሎት ለማከናወን የሚያስችል የአፈጻጸም መመሪያ አውጥቶ ሥራ ላይ ለማዋል እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በቬንደር ፋይናንሲንግ ኘሮግራም በመታገዝ  ከሚያካሂዳቸው ግዙፍ የቴሌኮም ኔትወርክ ዝርጋታዎች ውስጥ በዋነኝነት የሞባይል አገልግሎትን እና የCDMA 2000 ገመድ አልባ የቴሌፎን አገልግሎቶችን uመላ አገሪቱ  ለማዳረስ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህንንም ጥረት ለማሳካት ኮርፖሬሽኑ የቅድመ ክፍያ ሲም ካርዶችን ማለትም የመደበኛ /GSM ሞባይል፣ የ3G WCDMA ሞባይል እና የባለሙሉ ተንቀሳቃሽ የCDMA 2000 - ቴሌፎን እንዲሁም የማስደወያ ካርዶችን በተለያዩ የንግድ ተቋማትና ማህበራት አማካይነት ለደንበኞች በውክልና የማከፋፈል/ የሽያጭ አገልግሎት ለማከናወን የሚያስችል የአፈፃፀም መመሪያ አውጥቶ ሥራ ላይ ለማዋል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ 

የአፈጻጸም መመሪያ ዓላማው ኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ እያደረገ ያለውን መጠነ ሰፊ የኔትወርክ ዝርጋታ መሠረት በማድረግ የሚደርሰውን ተጨማሪ የቅድመ ክፍያ አገልግሎቶች ሽያጭ አሁን በኮሚሽን ክፍያ እየሠሩ ካሉ ጥቂት ወኪል ድርጅቶች በተጨማሪ በየክልል ከተሞች በየአቅራቢያው በሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ወኪል ድርጅቶች በኩል ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ ደንበኛው የተለያዩ የቅድመ ክፍያ ካርዶች በአገርአቀፍ ደረጃ በቅርብ ርቀትና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያገኝ ማድረግ እንዲሁም ካርዶቹን በውክልና እንዲሸጡ በማድረግ ኮርፖሬሽኑ በዋነኛ ሥራው ላይ ለማተኮር እንዲያስችለውና ለደንበኛውም በተቀላጠፈ መንገድ አገልግሎቱን ለመስጠት እንዲያስችለው ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ከቅድመ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኛ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የካርድ ፍላጎት በመጨመሩ እንዲሁም ቫውቸር ካርዶችን ለማከፋፈል ከድርጅቶች ወይም ከማኀበራት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ባለመቻሉ እና የካርድ ሽያጭ ገቢ አሰባሰብ በጥሬ ገንዘብ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የገንዘብ ደህንነት ስጋት በመኖሩ የተነሳ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

በዚህ የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በውክልና የሚሸጡ የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ካርዶች የሚከተሉት ናቸው:-

o የቅድመ ክፍያ GSM፣ WCDMA /3G/ ሞባይል እና የባለ ሙሉ ተንቀሳቃሽ CDMA-2000 ቴሌፎን ሲምካርዶች
o ለቅድመ ክፍያ GSM እና WCDMA /3G/ ሞባይል አገልግሎቶች ማስደወያ የሚያገለግሉ ስክራቸብል/ ቫውቸር ካርዶች፤
o ለገጠር መገናኛ ዋየርለስ እንዲሁም ለገጠር እና ከተሞች መገናኛ የሚሆኑ የCDMA-2000 /ፊክስድና ሞባይል/ ማስደወያ የሚያገለግሉ የኘላስቲክ ቫውቸር ካርዶች እና
o በህዝብ ቴሌፎን ለመደወል የሚያስችሉ ስክራቸብል ካርዶች /Smart cards/ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

አንድ ወኪል ድርጅት ሲም ካርድ ከኮርፖሬሽኑ በጅምላ በሚገዛበት ወቅት 8% ኮሚሽን የሚታሰብለት ማለትም ከኮርፖሬሽኑ የሚገዛበት ዋጋ ከደንበኝነትና ከአየር ጊዜ ዋጋ ላይ ኮሚሽን በመቀነስ ተጨማሪ እሴት ታክስና የቀረጥ ቴምብር በመደመር ይሆናል፡፡
ለምሳሌ፡-
የመደበኛው የGSM ሞባይል እና የባለሙሉ ተንቀሳቃሽ CDMA 2000 ቴሌፎን ቅድመ ክፍያ ሞባይል ሲም ካርድ ለተጠቃሚ ደንበኞች የሚሸጥበት ከፍተኛ ዋጋ ብር 169.10 የሚያካትተው፡-
• የደንበኝነት ዋጋ Subscription fee ብር 120.96
• የአየር ጊዜ Air Time ብር 21.74
• ከደንበኝነትና ከአየር ጊዜ ዋጋ ላይ የሚታሰብ 15% ተ.እ.ታ VAT ብር 21.40
• የቀረጥ ቴምብር ብር 5 ሲሆን፣ ለወኪል ድርጅቶች የሚታሰበው 8% ኮሚሽን /ከተ.እ.ታ VAT በፊት/ ባለው የደንበኝነትና የአየር ጊዜ ዋጋ ድምር 142.70 ላይ 8% ማለትም በያንዳንዱ ሲም ካርድ  11.42 ብር ይሆናል ማለት ነው፡፡ 

በዚህ ሥራ ለመሠማራት ጥያቄ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ወይም ማህበራት ማሟላት ከሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ወይም መስፈርቶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው:-

o የቅድመ ክፍያ ሲም ካርድን በውክልና ለማከፋፈል ጥያቄ የሚየቀርቡ ድርጅቶች ወይም ማህበራት ከአዲስ አበባ ከሆኑ ካፒታሉ ብር 100,000 አንድ መቶ ሺህ እና ከዚያ በላይ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚቀርብ ጥያቄ ደግሞ 5ዐ,ዐዐዐ /ሃምሳ ሺህ/ ብርና ከዚያ በላይ ሆኖ ከዋናው /ኦሪጅናል/ ጋር የተገናዘበ የዘመኑ ግብር የተከፈለበት /የታደሠ የንግድ ፈቃድ ኮፒ እንዲሁም የንግድ ፈቃድ ማቅረብ የማይችሉ ድርጅቶች/ማህበራት የሥራ ፈቃድ፣ መመሥረቻ ሰነድና የምዝገባ ሰርተፊኬት ከኦሪጅናሉ ጋር የተገናዘበ ኮፒ ማቅረብ፣

o የቅድመ ክፍያ ማስደወያ ካርዶችን በውክልና ለማከፋፈል ጥያቄ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ወይም ማህበራት ከአዲስ አበባ ለሚቀርብ ጥያቄ ብር 5ዐ,ዐዐዐ /ሃምሳ ሺህ ብር/ እና ከዚያ በላይ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚቀርብ ጥያቄ ደግሞ ብር 25,ዐዐዐ /ሃያ አምስት ሺህ/ እና ከዚያ በላይ ሆኖ ከዋናው/ኦሪጅናል ጋር የተገናዘበ የዘመኑ ግብር የተከፈለበት/የታደሰ የንግድ ፈቃድ ኮፒ እንዲሁም የንግድ ፈቃድ ማቅረብ የማይችሉ ድርጅቶች ወይም ማህበራት የታደሠ የሥራ ፈቃድ፣ የመመስረቻ ሰነድና የምዝገባ ሰርተፊኬት ከኦሪጅናሉ ጋር የተገናዘበ ኮፒ ማቅረብ፣

o የቅድመ ክፍያ ማስደወያ ካርዶችን በውክልና ለማከፋፈል ከአካባቢው መስተዳድር የድጋፍ ደብዳቤ የሚያቀርቡ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና የመሳሰሉት ያለባቸውን የአቅም ውሱንነት ከግምት በማስገባትና የሥራ ዕድልን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ከመደገፍ አንፃር ከላይ የተጠቀሰውን ካፒታል ሳይጠየቁ ከኦሪጅናል ጋር የተገናዘበ የማህበራቸውን መመሥረቻ ሰነድና የምዝገባ ሰርተፊኬት ኮፒ በማቅረብ በሥራው ላይ መሰማራት ይችላሉ፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ አንድ ድርጅት ወይም ማህበር በሀገሪቱ ውስጥ በተመደበለት መልከዓ ምድራዊ ወይም ጂኦግራፊያዊ አካባቢ በውል በተገደበው መሠረት የቅድመ ክፍያ ሞባይል ሲም ካርድ የመልሶ ሽያጭ ወይም የማከፋፈል ሥራ እንዲያከናውን ከኮርፖሬሽኑ ውክልና ሲሰጠው ተወካዩ የሚከተሉትን ግዴታዎች መፈጸም ይጠበቅበታል፡-

 ወኪል አከፋፋዩ የሲም ካርድ የመሸጫ ዋጋን በሽያጭ ማዕከላት በግልጽ በሚታይ ቦታ ጽፎ የመለጠፍ ግዴታ አለበት፡፡
 ኮርፖሬሽኑ ካስቀመጠው የሲም ካርድ ታሪፍ በላይ መሸጥ ወይም ማከፋፈል እንዲሁም በገበያ ውስጥ ሰው ሰራሽ የሲም ካርድ እጥረት ለመፍጠር በማሰብ ሲም ካርድ ማከማቸት በህግ ያስጠይቃል፡፡
 ወኪል አከፋፋዩ ማናቸውንም አስፈላጊ የቴክኒክና መረጃ የመስጠት ድጋፍ ለደንበኞቹ የማድረግ ግዴታ ያለበት ሲሆን ከደንበኞቹ ቅሬታ በሚነሳበት ወቅትU የማጣራትና ችግሩን የመፍታት ኃላፊነት አለበት፡፡
 ወኪል አከፋፋዩ ውል የሚገባው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለመሸጥ ከሆነ ቢያንስ 100 /አንድ መቶ/፣ ከክልሎች ከሆነ 50 /ሃምሳ/ እና ከማህበራት ከሆነ 25 /ሃያ አምስት/ ሲም ካርዶችን እና ወይም ዝቅተኛ መጠኑ የብር 12,500 /አስራ ሁለት ሺህ አምስት መቶ/ ሆኖ ከፍተኛው መጠን ደግሞ የአንድ ሚሊዮን ብር የቅድመ ክርፍያ ማስደወያ ካርዶችን ወይም ቫውቸር ካርዶችን በአንድ ጊዜ መግዛት የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ክፍያውንም በባንክ በተመሰከረለት ቼክ ወይም ሲፒኦ ይፈጽማል፡፡
 ወኪል አከፋፋዩ የቅድመ ክፍያ ሞባይል ሲም ካርዶችን ለደንበኞቹ ከመሸጡ በፊት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያላበቃ መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡ የሲም ካርድ የአገልግሎት ጊዜ የፀና የሚሆነው ቁጥሮች ማዞሪያ ላይ ከተጫኑ ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስራ ሁለት ወራት ውስጥ ነው፡፡
 ወኪል አከፋፋዩ የቅድመ ክፍያ የሞባይል ሲም ካርድ አከፋፋይነት ውል  የተሰጠውን የስራ እንቅስቃሴ አፈጻጸም በተመለከተ ወርሃዊ ሪፖርት ለኮርፖሬሽኑ ያቀርባል፡፡
 ወኪል አከፋፋዩ የቅድመ ክፍያ ሞባይል የሲም ካርድ ሽያጭን በሚያከናውንበት ወቅት የደንበኞች ሙሉ ስም /የአያትን ስም ያካተተ/ እና አድራሻ መዝግቦ መያዝ ይኖርበታል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ቫውቸር ካርዶችን እየገዙ በማሰራጨት ላይ ያሉ በርካታ ጅምላ ነጋዴዎች ወይም ድርጅቶች ደግሞ በ200 እና 100 ብር ቫውቸር ካርዶች በተሸጠው መጠን ላይ የ10%  ኮሚሽን እንዲሁም በ50 እና 25 ብር ቫውቸር ካርዶች ላይ ደግም የ7% የኮሚሽን ክፍያ እየታሰበላቸው ለደንበኞች እንዲከፋፈሉ እየተደረገ ይገኛል::

በአሁኑ ወቅት በዞን እና ሪጅን ጽ/ቤቶች አማካኝነት ውል ተፈራርመው የሞባይል ቅድመ ክፍያ ካርድና ስማርት ካርድ የሽያጭ ሥራ ላይ የተሰማሩ ብዛታቸው ከ12 ሺህ በላይ የሚደርሱ የችርቻሮ ነጋዴዎች ያሉ ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉት እነዚህ የችርቻሮ ነጋዴዎች ኮርፖሬሽኑ ባዘጋጀው የአፈፃፀም መመሪያ ውስጥ የተቀመጡትን መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሆኑና በዘርፉ መሰማራት ከፈለጉ ጥያቄያቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ዞን ወይም ሪጅን ጽ/ቤቶች ወይም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በማቅረብና ውል በመፈራረም ካርድ በማከፋፈሉ ስራ ላይ መሠማራት ይችላሉ፡፡   

የቅድመ ክፍያ ማስደወያ ካርድ ለማከፋፈል ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል የሚገቡ ድርጅቶች ወይም ማህበራት በሥራቸው የሚቋቋሙ የችርቻሮ የሽያጭ ማዕከላትን ለመለየትና ቅሬታም ሲኖር ለማወቅ የሚያስችል የኮርፖሬሽኑን አርማ እና ማህተም ጨምሮ የመለያ ኮድ ቁጥርና የኮርፖሬሽኑና የወኪሉን የቴሌፎን ቁጥር ያካተተ ታፔላ  /መለያ ኮድ/ ተዘጋጅቶ በወኪሉ የሽያጭ ቢሮ እንዲለጠፍ ይደረጋል፡፡
 
ቀደም ሲል ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል በመፈጸም በውክልና የሲም ካርድ በሚያከፋፍሉ ሜጋ ዲለሮች እና ቫውቸር ካርድ በሚያከፋፍሉ የችርቻሮ ነጋዴዎች በኩል የሚከናወነው የውክልና ሽያጭ አሁን በተደረገው የአሰራር ለውጥ መመሪያ መሠረት በቂ የሲም ካርድ እና የቫውቸር ካርድ ስርጭት በገበያ ላይ መኖሩ እስከሚረጋገጥ ድረስ ለጊዜው ባለበት ሁኔታ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡

 በኮርፖሬሽኑና በወኪል ድርጅቶች መካከል የሚኖረው የስራ ግንኙነት በዋነኛነት የቅድመ ክፍያ ሞባይል ሲም  ካርድ እና ቫውቸር ካርዶችን መሸጥ፣ ከሲም ካርድ ወይም ቫውቸር ካርድ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ሙያዊ ወይም የቴክኒክ ድጋፍ ለደንበኞች መስጠት እና ከተጠቃሚ ደንበኞች ቅሬታዎች ሲቀርቡ ክትትል በማድረግ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን!
ታህሳስ 13 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.


 
 
 
 
 
 
 
 
Copyright© 2009 Ethiopian Telecommunications Corp. All rights reserved!