ETC News    
   
     WHO IS WHO
     CHECK MAIL
     VACANCY
     YELLOW PAGES
     FEEDBACK
     FAQs
 
Dialing Codes
   
Interurban Dialing Code
  Essential Numbers
  International Dialing Codes
 
Websites at Ethiopage
   
 
 
 
  ኮርፖሬሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሔደ
January 20, 2010

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማስፋፋት ረገድ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የምክክር መድረክ ታህሳስ 27 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል አካሔደ፡፡

በዕለቱ የተካሔደውን የምክክር መድረክ አስመልክተው በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዋና ክፍል ጊ/ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ለገሠ እንደገለፁት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንደቀድሞ ዘመናት የቅንጦት መገልገያ ሳይሆን የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት እየሆነ መምጣቱን ገልፀው፣ ዘርፉን በቀጣይ ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ለማስቻል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመቀጠልም የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ /ኦኘሬሽንስ/ አቶ ተስፉ ገ/ሚካኤል የመድረኩን አስፈላጊነት አስመልክተው እንዳሉት፣ መድረኩ በዋነኛነት ኮርፖሬሽኑ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት በማስፋፋት በመረጃ የበለፀገ ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት ግቡን እንዲመታ እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ተቀራርቦ ለመስራት እንዲቻል እንዲሁም  በአይ.ሲ.ቲ /ICT/ ዘርፍ የታዩትን የአዳዲስ አገልግሎቶች ግብዓት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍና ከዘርፉ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ብሎም ከውጭ በሚመጡ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች እና ተዛማጅ የኤሌክትሮኒክ መገልገያዎች ከቀረጥ እና ከጥራት አንፃር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን እንዲሁም እነዚህን መሳሪያዎች ለማስገባት ሀገሪቱ በፖሊሲ ደረጃ የምትከተለውን የቀረጥ አጣጣልና የጥራት ሁኔታ መቃኘት ነው፡፡

በተጨማሪም የመሣሪያዎቹ አቅራቢ የሆነውን የግል ዘርፍ ለማበረታታት መንግስት የሚሠጠውን ድጋፍና በንግዱ ማህበረሰብ በኩል መሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች በተመለከተ በግልጽ ለመወያየት እና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኮርፖሬሽኑ በቀጣዩ ትውልድ ኔትወርክ ማስፋፊያ ኘሮግራም አማካኝነት እያካሔዳቸው ያሉትን ግዙፍ እና ዘመናዊ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታዎች የስራ ሂደት ለታዳሚዎች የገለፁ ሲሆን፣ አክለውም አገልግሎቶቹን በስራ ላይ ለማዋል ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ጊዜያቶች የሚያወጣቸው የደንበኝነት ምዝገባ /Subscription/ እና የመጠቀሚያ ዋጋ ተመጣጣኝ ካልሆነ፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ መጠቀሚያ መሳሪያዎች ወይም ቀፎዎች እንደ መደበኛ ስልክ በጥራትና በበቂ መጠን ገበያ ላይ ካልተገኙ እንዲሁም ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር ተመጣጣኝ ካልሆኑ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተዘረጋውን የኔትወርክ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል አዳጋች እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የተጠቀሱትን ማነቆዎች ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ ጥቅም ላይ የዋለውን ሰፊ የኔትወርክ አቅም በመጠቀም የህብረተሰቡን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ /ICT/ ፍላጎት ለማርካት በጋራ መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዕለቱ በተካሔደው የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላቶች ያሉዋቸውን ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ የቴሌኮም መጠቀሚያ መሳሪያዎችን ለሚያስገቡ ድርጅቶች ፍቃድ የሚሰጥ ቢሆንም ፍቃድ ያገኘው ድርጅት የተሟላ የጥገና ስራ ማከናወን አለማከናወኑን ሲከታተል አይስተዋልምና ኤጀንሲው ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጥ፣ ኮርፖሬሽኑ ከአገልግሎት አቅራቢነት ውጪ የሌሎች አገልግሎቶችን ሽያጭ ባያከናውን፣ የቴሌኮም መገልገያ እቃዎችን ከውጭ ሀገር በሚያስገቡበት ወቅት የሚቀርበው የቀረጥ ጥያቄ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያም ሆኖ በገበያ ውስጥ ገብተው ህብረተሰቡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ እቃዎችን ስለሚጠቁም ለኪሳራ መዳረጋቸውን፣ እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እየሰጠ ስላለው የቴሌኮም አገልግሎት ሽፋን የተሟላ መረጃ ቢሰጣቸው አስፈላጊውን መገልገያ መሳሪያ ለማስገባት ስለሚረዳቸው በዚህ በኩል ኮርፖሬሽኑ ቢንቀሳቀስ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ለሀገሪቱ ኔትወርክ ተስማሚ የሆኑ የማዞሪያ /PBX/ ቀፎዎች የትኞቹ እንደሆኑ የቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ የጥራት መመዘኛ /Specification/ አውጥቶ በፍጥነት ቢያሳውቃቸው ጥራት ያላቸውን ቀፎዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ስለሚረዳቸው ኤጀንሲው እንዲያጤነው፣ ኮርፖሬሽኑ ወደ ሀገር የሚገቡ የስልክ ገመዶችን /Cables/ ጥራት እንዴት ይመለከታል? በከተሞች ውስጥ በሚስተዋሉ የኮንትሮባንድ የሞባይል እና መደበኛ ስልክ ቀፎዎች አቅርቦት ዙሪያ የሚመለከተው አካል ቁጥጥር ቢያደርግ፣ አዲስ በሚገነቡ ህንፃዎች ውስጥ የሚካሔዱ የማዞሪያ /PBX/ ስልክ መስመሮችን ለመዘርጋት ህጋዊ እውቅና አግኝተን ግብር እየከፈልን ያልታወቁ ግለሰቦች ጥራት የጐደለው አገልግሎት እያቀረቡ በመሆኑ ቁጥጥር ቢደረግ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም በዘርፉ ጥናት ማካሔዳቸውን የገለፁ ተሳታፊ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት 3.5 ሚሊዮን ሲም ካርዶችን ቢሸጥም በህጋዊ መንገድ ታክስ ተከፍሎባቸው በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የሞባይል ቀፎዎች ብዛት 44,2ዐዐ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይህ ሁኔታ በህጋዊ መንገድ ግብር እየከፈሉ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሀብቶችን እየጐዳ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እንደተሳታፊው ገለፃ ከሆነ በተለያዩ ጊዜያቶች በተለይም በተጠቀሱት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኮንትሮባንድ ከገቡ የሞባይል ስልክ መጠቀሚያ ቀፎዎች መንግስት ቀረጥ ቢሰበስብ እስከ 2ዐዐ ሚሊዮን ብር ድረስ ግብር ማግኘት በቻለ ነበር ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም የችግሩን አሳሳቢነት ተመልክቶ መንግስት አስፈላጊውን ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል ሲሉ በአጽንኦት አስረድተዋል፡፡

በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ላይ የኮርፖሬሽኑ ም/ዋ/ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፉ ገ/ሚካኤል ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና አላማ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ ተመጣጣኝነት ያለው እርካታ መፍጠር መሆኑን ገልፀው፣ በቀጣይ ኮርፖሬሽኑ የነደፋቸው በርካታ ዓላማዎች እንዳሉ ዓላማዎቹንም ከዳር ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚሁ የምክክር መድረክ ላይ አቶ ውብነህ እምሩ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሠረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ልማት ኤጀንሲ እና ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የተለያዩ የስራ ክፍሎች የተወከሉ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም በኮርፖሬሽኑ የተጋበዙ በርካታ በዘርፉ የተሰማሩ የቴሌኮም መሳሪያ አቅራቢዎች እና የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በዕለቱም ጠቃሚ ጽሁፎች እና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት እና ምክክር ተካሒዷል፡፡


 
 
 
 
 
 
 
 
Copyright© 2009 Ethiopian Telecommunications Corp. All rights reserved!