ጋዜጣዊ መግለጫ
ኢትዮ ቴሌኮምና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎች ምዝገባ አሠራር ሥርዓት በሥራ ላይ እንዲውል አደረጉ
ኢትዮ ቴሌኮምና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎችን ምዝገባ ለማከናወን የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት በሥራ ላይ እንዲውል አደረጉ፡፡
እስከአሁን ደንበኞች እየተጠቀሙባቸው የሚገኙ የሞባይል አገልግሎት መጠቀሚያ ቀፎዎች በሲስተም ላይ ተመዝግበዋል አገልግሎቱንም መጠቀም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በደንበኞች እጅ የሚገኙ እና በተለያየ ምክንያት እየተጠቀሙባቸው የማይገኙ የሞባይል እና ሌሎች በሲም ካርድ የሚሠሩ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች የኩባንያው ኔትዎርክ ውስጥ ባለመመዝገባቸው እና ኔትወርኩ ስለማያውቃቸው ደንበኞች በእጃቸው ላይ የሚገኙ እና በተለያየ ምክንያት እየተጠቀሙባቸው የማይገኙ ከላይ የተጠቀሱትን የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎችን እስከ መስከረም 07 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ መሣሪያዎቹ ላይ ሲም ካርድ በማስገባት እና ከኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርክ ጋር በማገናኘት ሲስተም ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህ የተንቀሳቃሽ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች የመለያ ቁጥር ምዝገባ የሚካሄደው በቀጥታ በኩባንያው የኔትወርክ ሲስተም ላይ በመሆኑ ደንበኞች እነዚህን የተጠቀሱትን እየተጠቀሙባቸው ያሏቸውን የቴሌኮም መገልገያ ቁሳቁሶች እስከ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ሲም ካርድ አስገብተው እንዲሰሩ ማድረግ ብቻ በቂ ሲሆን ለማስመዝገብ ወደ ኩባንያው ጽ/ቤቶች ይዘው መምጣት አይጠበቅባቸውም፡፡
ይህ የምዝገባ ሂደት ያስፈለገበት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ባደጉ ሀገራትና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር እየተተገበረ ያለ ዘመናዊ አሰራር በመሆኑ ሲሆን በተለይም ተገልጋዩን ደንበኛ ከሥርቆት ጋር በተያያዘ የሚደርሱ ተያያዥ ጉዳቶችን ለመከላከል ሲሆን በተለይ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ስልኮች የሚያስከትሉትን የአገልግሎት ጥራት መጓደል እንዲሁም ተመሳስለው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ህገ ወጥ ስልኮች አማካኝነት እየደረሰ ያለውን የአገልግሎት ጥራት ችግርና የወንጀል ጉዳት ለመከላከል እንዲሁም በህጋዊ አስመጪዎችና በሀገር ውስጥ ሞባይል ቀፎዎችን ገጣጥመው ለገበያ በሚያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ እየተፈጠረ ያለውን አግባብነት የሌለው የገበያ ውድድር ለማስቀረት ነው፡፡
በተጨማሪም በየግዜው ከሚፈጸም የሞባይል ስርቆትና ይህንን ተከትሎ በተሰረቁ የሞባይል ስልኮች አማካኝነት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ነው፡፡
በመሆኑም በተለይም በሃገራችን በህጋዊ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ እና ኦሪጅናል የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች የመኖራቸውን ያህል ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ጥራታቸውንና ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ኦሪጅናል ምርቶች ያልሆኑ መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ እየዋሉ ይገኛል፡፡ በዚህ ህገወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች የህብረተሰቡን የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚነት ፍላጎትና ጉጉት በመመልከት ጥራት የሌላቸው፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ በህብረተሰብ ጤና እና ምርታማነት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እንዲሁም በሃገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ምርቶችን በተለያዩ መንገዶች ወደሃገር ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ ጉዳት በሃገርና በህብረተሰቡ ላይ እያደረሱ ይገኛል፡፡
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ እና ደረጃቸውንና ጥራታቸውን ያልጠበቁ የቴሌኮም መጠቀሚያ ቁሳቁሶች አገልግሎት ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ተከትሎ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴከኖሎጂ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች ቁጥጥርና ምዝገባ ለማካሄድ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ላይ ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ይህን መመሪያ ስራ ላይ አውሏል፡፡
ይህንን መመሪያ መሰረት በማድረግም ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ ምዝገባ አሠራር ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች በሚተገብሩት መሠረት ይህን ዘመናዊ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በተለይም ይህን በደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት ላይ፣ በአምራቾችና የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች አትራፊነት ላይ እንዲሆም በህብረተሰብ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ያለውን ጉዳይ በመሠረታዊነት ለመቅረፍ የሚያስችለውን ተንቀሳቃሽ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎችን በኔትወርክ አማካኝነት በቀጥታ የመመዝገብ ሥራ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ይህ የቀጥታ የምዝገባ ሂደት በተለያዩ መንገዶች ወደ ሃገር ውስጥ በሚገቡ፣ ደረጃቸውን ባልጠበቁ እና ኦሪጅናል ባልሆኑ የሞባይል (የተንቀሳቃሽ) ስልኮችና ሌሎች ሲም ካርድ በሚቀበሉ መሣሪያዎች መበራከት የተነሳ በደንበኞች የሞባይል ስልኮች አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እና ጉዳት የሚደርሰውን ችግር ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ይህ ችግር በዘላቂነት መፈታቱ ወደ ሃገራችን በህገወጥ መንገድ በሚገቡ እንዲሁም ኦሪጅናል ባልሆኑ እና በተሰረቁ የሞባይል ቀፎዎች ምክንያት ለችግር እንዳይዳረጉ ለማድረግ ያስችላል፡፡
ተንቀሳቃሽ የሆኑ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎችን በኔትወርክ አማካኝነት በቀጥታ የመመዝገብ ሂደት ዋና ዋና ፋይዳዎች/ጥቅሞች
- ሃገሪቱ ከኦሪጅናል ምርቶች ቀረጥ የምታገኘውን ገቢ ያሳድጋል፤
- በኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኔትወርክ ውስጥ ያሉ ሁሉንም የሞባይል ተጠቃሚዎችን ባሉበት ለመለየት ያስችላል (Automatic real-time device detection)፤
- ህገወጥ የሆነ ወይም ፈቃድ ያላገኘ ተንቀሳቃሽ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሣሪያ ኔትወርክ እንዳይጠቀም ለማድረግ ያስችላል፤
- የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሣሪያን በባለቤቱበደንበኛው ስም በዝግቦ ለመያዝ ያስችላል።
ለኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የሚኖረው ጥቅም
- የተሰረቁ ተንቀሳቃሽ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሣሪያዎች ጥቁር መዝገብ (ብላክሊስት) ውስጥ እንዲገቡ እና በኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ያስችላል፤
- ደንበኞች ኦሪጅናል እቃዎችን መርጠው በመግዛት አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ደንበኞች ግዢ ከመፈፀማቸው በፊት እቃዎቹ ኦሪጅናል መሆናቸውን ሲም ካርድ በማስገባት ማረጋገጥ ይችላሉ፤
- በደንበኞች ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ ቁሳቁሶች ከገበያ እንዲወጡ ለማድረግ ያስችላል፤
- ኦሪጅናል ዕቃ በመጠቀማቸው ምክንያት ደንበኞች አስተማማኝ/ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ፤
- ኦሪጅናል ዕቃ የሚጠቀሙ ደንበኞች የሚገዟቸውን የቴሌኮም መጠቀሚያ ቁሳቁሶች ረዘም ላለ ጊዜ የመጠቀም ዕድል ይኖራቸዋል፤
- ደንበኞች ለመለዋወጫ ዕቃዎች እና ለጥገና የሚያወጡትን ወጪ በእጅጉ ይቀንስላቸዋል፤
ለአስመጪዎችና ለአምራቾች ያለው ጠቀሜታ
- በሚታወቁ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ ሥራቸውን በሚያከናውኑ አስመጪዎችና አምራቾች መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር እንዲኖር ያስችላል፣
- አስመጪዎችና አምራቾች የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ያነሳሳቸዋል፣
- የማምርት አቅምና የሽያጭ መጠን (Production capacity and Sales volume) ለማሳደግ ያስችላቸዋል፣
- በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ለሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ አስተማማኝ ገቢ ይኖራቸዋል (Good return on investment)
- ህገወጥ የሆነ የግብይት ሂደት እየተዳከመ ይሄዳል፤
- የሃገር ውስጥ አምራቾች ደንበኞችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የፈጠራ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል፡፡
ለሃገር ያለው ፋይዳ
- በህጋዊ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ ከሚገቡ ምርቶች በአግባቡ ቀረጥ እንዲሰበሰብ ያስችላል፤
- የሃገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል ለዜጎች ይፈጠራል፤
- ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ይወጣ የነበረ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ለማስቀረት ያስችላል፤
- ባለሃብቶች በሃገር ውስጥ ለማምረት ተነሳሽነት ስለሚኖራቸው ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት ይረዳል፡፡ በአጠቃላይ የሃገሪቱ የቴሌኮም እንቅስቃሴ ጤናማነት ላይ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል፡፡